የ2009 በጀት ዓመት የሠራተኞችና ባለአክሲዮኖች ዓመታዊ በዓል ተከበረ

የፀሐይ ኢንዱስትሪ አ.ማ. ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ የ 2009 በጀት ዓመት የሠራተኞችና ባለአክሲዮኖች ዓመታዊ በዓል ታህሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በድርጅቱ ቅፅረ ግቢ ውስጥ በድምቀት አከበረ፡፡ የድርጅቱ ዓመታዊ የሠራተኞች በዓል በተከበረበት ወቅት የፀሐይ ኢንዱስትሪ አ.ማ. ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ማቴዎስ አሰሌና የአክሲዮን ማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ፈንቴ ንግግር አድርገዋል፡፡ አቶ ማቴዎስ አሰሌ ባደረጉት ንግግር፡-

 • አክሲዮን ማህበሩ ቃሊቲ ብራታ ብረት ፋብሪካን በግዥ ከተረከበበት ሐምሌ 5 ቀን 2004 ዓ.ም አንስቶበየዓመቱ ፋብሪካው በዕድገት ጎዳና በመጓዝ ላይ የሚገኝ መሆኑን፣
 • በ2009 በጀት ዓመት የተመዘገበው ክንውን ከቀዳሚው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በምርት 0.6%፣ በሽያጭ የ11.3%፣ እንዲሁም በትርፍ የ78% ዕድገት ማሳየቱን፣
 • በበጀት ዓመቱ የገበያውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የተሳቢና የጭነት አካላት ምርትን በብዛት በማምረት ወደ ገበያው መገባቱን፣
 • ፋብሪካውን ለማስፋፋት ከተያዘው ዕቅድ አኳያ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን ለማካሄድ ይቻል ዘንድ ከብር 88 ሚሊዮን ያላነሰ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት መካሄዱን፣

ገልፀዋል፡፡
ይሁን እንጂ በበጀት ዓመቱ የውጭ ምንዛሬ በበቂ ሁኔታ አለመገኘቱ ከፍተኛ ችግር የነበረ ቢሆንም በነበረው ውስን ጥሬ ዕቃ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረትና በመሸጥ አፈፃፀሙ እንዳይጎዳ ለማድረግ መቻሉንና ይህ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ማነቆ ሆኖ ካልቀጠለ በስተቀር ለሚቀጥሉት የበጀት ዓመታት አፈፃፀሙን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ እንደሚቻል በበዓሉ ላይ ለታደሙት ሠራተኞችና ባለአክሲዮኖች አስረድተዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የተገኙት የአክሲዮን ማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ፈንቴ ባደረጉት ንግግርም፡-

 • አክሲዮን ማህበሩ ፋብሪካውን በግዥ ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ ውጤታማ ሊያደረጉ የሚችሉ በርካታ የአደረጃጀት የአሠራርና ሌሎች ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን፣
 • በባለአክሲዮኖችና በቦርዱ፣ በቦርዱና በማኔጅመንቱ እንዲሁም በማኔጅመንቱና በሠራተኞቹ መካከል በነበረው የአንድነትና የትብብር መንፈስ የተነሳ ፋብሪካው ውጥኑ እየተሳካ በዕድገት ጎዳና እየተጓዘ እንደሚገኝ፣ለዚህም ማሳያው አክሲዮን ማህበሩ ፋብሪካውን በግዥ ከተረከበበት ሐምለ 5 ቀን 2004 ዓ.ም አንስቶ እስከ 2009 በጀት ዓመት መጨረሻ የተደረሰበት የዕድገት ደረጃ፡-
  በምርት 102%፣
  በሽያጭ 130%፣
  በአጠቃላይ ሀብት 208%፣
  እንደሆነ ገልፀው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የድርጅቱን አፈፃፀም በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሳድጉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ለማከናወን ተችሏል ብለዋል፡፡
 • በዕለቱ የሠራተኞች ማህበር ሊቀመንበር ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሠራተኞችን በመወከል ለማኔጅመንትና ቦርዱ ስጦታ አበርክተዋል፡፡ በዕለቱ ከ500 በላይ የሚሆኑ የድርጅቱ ሠራተኞችና ከ200 ያላነሱ ባለአክሲዮኖች በበዓሉ ላይ ተገኝተው ዓመታዊ በዓላቸውን በደማቅ ሁኔታ አክብረዋል፡፡