የፀሐይ ኢንዱስትሪ አ.ማ. 9ኛ መደበኛ እና 5ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ

የፀሐይ ኢንዱስትሪ አ.ማ. 9ኛ መደበኛ እና 5ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ታህሣሥ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆቴል ተካሂዷል፡፡

በጉባኤው ላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ፈንቴ ጥሪውን አክብረው በጉባኤው ላይ የተገኙትን ባለአክሲዮኖች በማመስገን ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን በንግግራቸውም፡-

  • የዳይሬክተሮች ቦርዱ ቀደም ሲል በተዘጋጀው የአክሲዮን ማኅበሩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት ለ2012 በጀት ዓመት በዕቅድ የተያዙ ልዩ ልዩ ተግባራት በአግባቡ እንዲከናወኑ ለአክሲዮን ማኅበሩ ማኔጅመንት ተገቢውን አመራር የመስጠት፣ የመከታተልና ተገቢውን ድጋፍ የማድረግ ተግባር ማከናወኑን
  • ካለፉት ዓመታት በከፋ ሁኔታ በሀገራችን በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት የተነሣ በቂ ጥሬ ዕቃ ለመግዛት ካለመቻሉም በላይ በሀገራችንና በመላ ዓለም ከተከሰተው የኮረና ወረርሽኝ ምክንያት አብዛኛዎቹ የንግድ እቅስቃሴዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተገደበውና በእጅጉ ተቀዛቅዘው ስለነበር የምርት፣የሽያጭና የትርፍ አፈፃፀም ከዕቅዱ ያነሰ ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ የችግሩን መጠን ለመቀነስ ይቻል ዘንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትና ማኔጅመንቱ ከግልና ከመንግስት ባንኮች ጋር በፈጠርነው ጠንካራ ግንኙነትና ክትትል የተነሣ በተገኘው አነስተኛ የውጭ ምንዛሪ በተገዛው ጥሬ ዕቃ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶች ላይ በማተኮር ተመርተው በተቻለ መጠን ወቅታዊ በሆነ የገበያ ዋጋ እንዲሸጡ በመደረጉ አክሲዮን ማኅበሩ ትርፋማነት እንዲቀጥል የተደረገ መሆኑን፣
  • በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ቀን የነበረው የአክሲዮን ማኅበሩ ጠቅላላ ሀብት በ2009 ከነበረበት ብር 941.438 ሚሊዮን ወደ ብር 1,135.84 ሚሊዮን ማደጉን ገልፀዋል፣
  • በዕለቱ፡

    • የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት እና ጌታቸው ዋቅጅራና ጓደኞቹ የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎችና የተፈቀደለት ኦዲተር አማካይነት የውጭ ኦዲት ሪፖርት ለተሰብሳቢዎች ቀርቦ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ፀድቀዋል፣
    • በ5ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤወው ደግሞ የአክሲዮን ማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ እና መመስረቻ ፅሑፍ ላይ የቀረበው የማሻሻያ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ውይይት ተደርጎ እንዲፀድቅ ተደርጓል፣